የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የስልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አዲስ የተዘጋጁ የአሰልጣኞች፣ የሰልጣኞች የሥነምግባር ማኑዋል እና የሬጅስትራር አሰራር ስርዓት ላይ ከአሰልጣኞች ጋር ውይይት ተከሄዷል፡፡ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዲስ ያዘጋጃቸው የአሰራር ማንዋሎች ተቋሙ በዘርፉ የመሪነት ሚናን በመወጣት ምሳሌ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ገልጸዋል፡፡ በተለይም አሰልጣኞች ውጫዊና ውስጣዊ ሥነምግባርን በመላበስ በተቋሙ ውስጥ ለተማሪዎቻቸው ጥሩ ምሳሌ በመሆን በሀገር ደረጃ ብቃት ያለው የቱሪዝም እና የሆቴል ባለሙያዎችን ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡

የሬጅስትራር ክፍል ኃላፊ አቶ አስፋው ዴረሳ በበኩላቸው አዲስ የሬጅስትራር አሰራር ሥርዓት መዘጋጀቱ ትክክለኛ የሰልጣኖች መረጃ እንዲኖር ለማድረግ፣ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ኢንዲሁም ለሚከሰቱ ችግሮች ተጠያቂነትን ለማስፈን ያስችላል ብለዋል፡፡
የሬጅስትራር የአሰራር ሥርዓት ማኑዋል የሬጅስትራር ስራዎችን በአግባቡ ለመምራት፣ ሰልጣኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ያልተሟላ የስልጠና ውጤቶችን ለማስተካከል የሚደረጉ ምልልሶችን በትክክል ለማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን መምህር ቲጃኒ ሁሴን ገልጸዋል፡፡
የአሰልጣኞች የሥነ ምግባር ማኑዋልን ያቀረቡት አቶ ታደሰ ሞላ የመምህራን አለባበስ ሥርዓት፣የስልጠና አሰጣጥ ሂደት፣የቤተ ሙከራዎች አጠቃቀም፣ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥበት አግባብና ሌሎችም የሥነምግባር ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የ2015 ትምህርት ዘመን የስልጠና ሂደት ዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡